constitutional interpretation

 

በሕገ  መንግስት ትርጉም  ላይ ለሕገ  መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የተሰጠ የሕግ አስተያየት (amicus curiae)

                                                                            ግንቦት 6 2012 ..

        አስተያየት አቅራቢ፡–     ታፈሰ ይርጋ  /መድህን

   የሕገ መንግስት ትርጉም ያስፈለገበት ነጥብ፤

የቅደመ ምርጫ እና ምርጫ በሚደረግበት ወቅት የአስቸኳያ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያስገደድ ሁኔታ ቢከሰት፣ በዚህም የተነሳ ምርጫ ማድረግ የማይቻል ቢሆን፣ የምርጫ ዘመናቸው ያበቃው ምክር ቤቶች እና የአስፈጻሚው አካል የሥራ ዘመን ምን ይሆናል ? ምርጫውስ የአስቸኳያ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው ክስተት ከተወገደ በኋላ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሊከናወን ይገባል?  ለሚሉት ጥያቄዎች ሕገ- መንገስቱ መልስ ስለማይሰጥ የሕገ መንስግስቱን አንቀጽ  54 (1)፣  አንቀጽ 58 (3) እና  93 ከሕገ-መንግስቱ ዓላማና ግቦች እንደዚሁም  ከመሰረታዊ  መርሆች ጋር በማስተሳሰር ትርጉም እንዲሰጣቸው የሚል ሲሆን የሚሰጠውም የሕግ አስተያየት የቀረበው  የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ትርጉም የስፈልገዋል ወይስ አያስፈልገውም የሚለውን ጭመር የሚያካተት መሆን አለበት የሚል ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሰውን የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ በአግባቡና በተሟላ ሁኔታ ለመመርመር እንዲቻል ቀጥሎ የተመለከቱተን ብሄራዊ፣ ዓለም-አቀፍ እና አህጉራዊ ሕጎችን ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡ አነዚህም፡-

ሀ) የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግስት  (ሕገ መንግስት)፣

ለ) የኢትዮጵያ የምርጫ ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 (የምርጫ ሕግ)

(ሐ) የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አዋጅ ቁጥር 798/2005፤

(መ) ዓለም-አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ፤ (Universal Declaration of Human Rights (UDHR) );

(ሠ) ዓለም አቀፍ የሰቪልና የፖለቲካ መብቶች ድንጋጌ፤  (International Covenant on Civil and Political Rights (ICCPR);

(ረ) በሴቶች ላይ የሚፈጸምን ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ለማስቀረት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወጣ  ኮንቬንሽን፤ (Convention to End All Forms of Discrimination against Women (CEDAW);

(ሰ) የአካል ጉዳተኞችን መብት ለመጠበቀ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወጣ አዋጅ፤  (Convention on the Rights of Persons with Disabilities (CRPD)

(ሸ) የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብት ቻርተር፤ (African Charter on Human and Peoples Rights (ACHPR).   

 

  አስተያየት፤

  1. የቀረበው ጉዳይ የሕገ መንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል ወይስ አያስፈልገውም የሚለውን ነጥብ በተመለከተ
    • በአዋጅ ቁጥር 1/1987 የታወጀው ሕገ-መንግስት በአንቀጽ 38 ስር የመመረጥና የመመረጥ መብትን ድንግጓል፡፡ በዚህም መሰረት፡-,

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም፣ በዘር፣ በብሄር ፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አመለካከት ወይም በሌላ አቋም ላይ የተመሰረተ ልዩነት ሳይደረግበት በቀጥታና በነጻነት በመረጣቸው ተወካዮች አማካኝነት በሕዝብ ጉዳይ የመሳተፍ፣ በማናቸውም የመንግስት ደረጃ በየጊዜው በሚካሄድ ምርጫ የመመረጥና የመመረጥ መብት እንዳለው፣  ምርጫውም ሁሉን አቀፍ ፣ በሁሉም እኩልነት ላይ የተመሰረተና በሚስጥር ድምጽ አሰጣጥ መራጩ ፈቃዱን በነጻነት የሚገልጸበት ዋስትና የሚሰጥ መሆን አለበት በማለት ደንግጓል፡፡ [1]  በተመሳሳይም የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባለት፣ ሁሉ አቀፍ ፣ ነጻ፣  ቀጥተኛ ፣ ትክክለኛ በሆነና በሚስጠር በሚሰጥበት ሥርዓት እንደሚመረጡ ሕገ-መንግስቱ ደንግጓል፡፡ [2]

1.2    የምርጫ ሕጉ [3] ማንኛውም ምርጫ ሁሉን አቀፍ፣ ቀጥተኛ፣ በምስጢር ድምፅ አሰጣጥ መራጩ ፈቃዱን በነፃነት የሚገልጽበት እና ያለ ምንም ልዩነት በሚደረግ ህዝባዊ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ ይሆናል በማለት ደንግጓል፡፡

1.3     ዓለም አቀፍ የምርጫ መለኪያዎች (international election standards) ምንጫቸው በአባል አገራት የተፈረሙ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አንደመሆናቸው መጠን ,በሁሉም አገራት ተፈጻሚ ሊሆኑ የሚገባ አጠቃላይ መርሆች ( Universal principles) ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አጠቃላይ የሰብዓዊ መብት መግለጫ (Universal Declaration of Human Rights (UDHR) ) “The will of the people shall be the basis of the Authority of Government ; this will shall be expressed in periodic and genuine elections which shall be by universal and equal suffrage and shall be held by secret vote or by equivalent voting procedures.”[4]  ይህም ወደ አማረኛ ሲተረጎም  “የሕዝብ ፍላጎት የመንግስት ሥልጣን መሰረት ነው፣  ይህም የሚገለጸው በየጊዜው፣ በሀቀኛነት፣ አጠቃላይ፣ ሁሉን አቀፍ እና በሚስጠር በሚሰጥ የደምጽ አሰጣጥ ምርጫ  ነው “ የሚል ነው፡፡

1.4   በዓለም-አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ድንጋጌም በተመሳሳይ አገላለጽ ተደንግጓል፡፡ [5] ሲሆን በአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብት ቻርተርም ይሄው ቃል በቃል ተንጸባርቋል፡፡ [6]

1.5     ሕገ መንግስቱ እና ሕገ መንግስቱን ተከትሎ የወጣው የምርጫ ሕግ እንደዚሁም አገሪቱ የተቀበለቻቸው ዓለም-አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶች ባልተለያየ ቃል ምርጫ መደረግ ያለበት ከላይ በተመለከተው አግባብ ስለመሆኑ ተደንግጓል፡፡

1.6    በሌላ በኩልም የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ከላይ በተመለከተው አግባብ ሁሉ አቀፍ ( ) ነጻ ፣ ቀጥተኛ ትክክለኛ ድምጽ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት አመቱ በሕዝብ እንደሚመረጡ በአንቀጽ 54 (1) ላይ የተደነገገ ሲሆን ይሄው የአምስት ዓመት ጊዜ ከመጠናቀቁ አንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ እንደሚጠናቀቅ ተደንጓል፡፡ [7]

1.7    የአስቸኳያ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀበት ምክንያትና ሥነ-ሥርዓቱ በአንቀጽ 93 ላይ የተደነገገ ሲሆን አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው ወረርሽኝ ሳቢያ በአንቀጽ 93 አግባብ የአስቸኳያ ጊዜ አዋጅ ታውጆ አገሪቱ በአስቸኳያ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ተገኛለች፡፡

1.8  ሕገ መንገስቱና ሕገ መንገስቱን ተከትሎ የወጣው የምርጫ ሕግ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ቀጠተኛ ሁሉ አቀፍ ምርጫ ሊደረግ እንደሚገባ የተቀበለ ሲሆን በዚህ ረገድ የወጡትን ዓለም አቀፍና አሁጉራዊ ስምምነቶችን አገሪቱ ተቀብላ የሕጓ አካል አድርጋቸዋለች፡፡ ሕገ መንግሰቱ የበላይ ሕግ ስለመሆኑ እንደዚሁም አገሪቱ የተቀበለቻቸው ዓለም-አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ ሕግ አካለት ሆነው አንደሚቆጠሩ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ (1) እና (4) ላይ ተመልክቷል፡፡

በአንድ በኩል  ሕገ መንግስቱ በአንቀጽ 54 (1) መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባለት ከላይ በተመለከተው አግባብ ሁሉ አቀፍ ፣ ነጻ ፣ ቀጥተኛና  ትክክለኛ ድምጽ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት አመቱ በሕዝብ እንደሚመረጡና ይሄው የአምስት ዓመት ጊዜ ከመጠናቀቁ አንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ እንደሚጠናቀቅም በአንቀጽ 58 (3) ላይ ሲደነገግ የአምስት ዓመቱ የመርጫ ዘመን መጠናቀቂያው ላይ ምርጫውን እንደ ሕገ መንግስቱ ፍላጎት ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማካሄዴ የማያስችል ሁኔታ በፈጠር ምርጫው ሊራዘም የሚችል ሰለመሆኑም ሆነ በምን ያህል ጊዜም ሊራዘም እንደሚችል መልስ ሳይሰጠው በዝምታ አልፎታል፡፡

ከአጠቃላይ የሕግ አተረጓጎም መርህ አንጻር ሕግ ግልጽ ሳይሆን በሚቀርበት ጊዜ ወይንም  ዕልባት ለመስጠት የሚያስፈልጉ ነገር ግን ሕጉ አንጠልጥሎ የተዋቸው ወሳኝ ነጥቦች በሚኖሩበት ጊዜ በትርጉም ሽፋን አዲስ ሕግ እንዳይወጣ ከፍ ያለ ጥንቃቄ በማድረግ መሰረታዊ የሕግ አተረጋጎም መርሆችን በመከተል ሊተረጎም ይችላል፡፡

ሕገ-መንግስቱ አንጠልጥሎ የተወው ጉዳይ ከፍ ያለ አገራዊ ፋይዳ ያለው እንደመሆኑ መጠን ዓለም የተቀበላቸውን የሕገ-መንግሰት መሰራታዊ መርሆችን በመከተል የተዘለለውን ክፍተት በትርጉም በመሙላት ሕገ-መንሰግቱ ነፍስ ሊዘራበት ይገባል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡

1.9   እዚህ ላይ አከረካራው ነጥብ ከሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 83 (1) አኳያ የሕግ መንግስት ጉዳይ ለትርጉም እንደዚሁም ከአዋጅ ቁጥር 798/2005 አንቀጽ 3 (2) (ሀ) እና (ለ) የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሕገ-መንግሰቱን ለመተርጎም ሥልጣን የተሰጠው ሕገ- መንግስታዊ ክርክር ኖሮ  በፍርድ ቤት ወይንም በአስተዳደር አካል በተሰጠ ውሳኔ ላይ ተመስርቶ (party based (disputants) ) በሚኖርበት ጊዜ  ስለሆነ በዚህ አግባብ የተሰጠ ውሳኔ በሌለበት ሁኔታ  ሕገ-መንሰግሰቱን ለመተርጎም  የሕገ መሰረት አይኖርም የሚለው አካራካሪ ነጥብ (bone of contention) ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ይሁንና በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 83 (1) ላይ የተጠቀሰው ሕገ-መንግስታዊ ክርክር (constitutional dispute) የሚለው ሐረግ ከአንቀጽ 84 (1) ጋር በጣምራ ሲነበብ የአርቃቂውን ሃሳብ መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ( በዚህ ላይ የሕገ-መንግስቱን ቃለ ጉባዔ መመልከትም ጠቃሚ ነው) ፡፡ አንቀጽ 84 (1) የሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ከሕገ-መንግስት ክርክር ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ሕገ-መንግስታዊ ጉዳዮችን ለማጣራት ሰፊ ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ በዚህ ላይ በሕገ መንግስቱና በአዋጁ መካከል ልዩነት አለ ቢባል ያለው ልዩነት ከሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 9 (1) የሕገ-መንግስት የበላይነት (constitutional supremacy) መርህ  አኳያ ሕገ መንግስቱ የበላይነት ይኖረዋል፡፡ በሌላ በኩልም በፍርድ ሊወሰን የማይችል በማንኛውም ጉዳይ (unjustifiable matter)  ላይ የሕገ-መንግስት ትርጉም ጥያቄ ከሕግ አውጪ ም/ቤቶች ወይም ከአስፈጻሚ አካል በአዋጅ ቁጥር 798/2005 አንቀጽ 3 (2) (ሐ) ለጉባዔው ሲቀርብለት ሕገ-መንግስቱን ለመተርጎም ሥልጣን የተሰጠው መሆኑ ሲታይ ደግሞ አዋጁ በሕገ-መንገስቱ አንቀጽ 84 (1) መሰረት የተቀረጸ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡

በመሆኑም ትርጉም ያስፈልጋቸዋል የተባሉት የሕገ መንግስቱ ድንጋጊዎች ከሕገ መንግስቱ መግቢያ ጀምሮ አጠቃላይ ድንጌዎችን እና መሰረታዊ የሆኑ የሕግ መንግስት አተረጓጎም መርሆችን በመከተል አገሪቱ ከተጋረጠባት ሕገ-መንገስታዊ ቀውስ ለመውጣት ሕገ መንግስቱ ሊተረጎም ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡

  1. ሕገ መንገስቱ መተርጎም አለበት ከተባለ በምን መልኩ መተርጎም አለበት የሚለውን በተመለከተ፤2.1 አገራችን ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማድርግ በዝግጅት ላይ እንዳለች መላው ዓለምን ከፍተኛ ሥጋት ላይ የጣለ ወረርሽኝ ተከስቷል፡፡ በሽታው ወረርሽኝ ስለመሆኑም በዓለም የጤና ድርጅት ተረጋግጧል፡፡

በአገራችንም ወረርሽኙ የተከሰተ ከመሆኑም በላይ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 93 መሰረት የአስቸኳያ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከላይ የጠቀስናቸውና በዓለም አቀፍ ደራጃ ተቀባይነት ያለቸውና የእኛም ሕገ መንግስት እና የምርጫ ሕጉ የተቀበላው  ዓለም አቀፍ የምርጫ መለኪያዎች (international election standards) መሰረት ምርጫ ቀጠተኛና ሁሉ አቀፍ (universal suffrage ) መሆን ይገባዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ብሄራዊ፣ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ  ሕጎች  በሙሉ ምርጫ በዚህ አግባብ መከናውን እንዳለባቸው የደነገጉ ሲሆን ዓለመም የተቀበለው ነው፡፡ የመመረጥ ችሎታ ያላቸው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ( ወንዶች፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን እና ሌሎችም የኅብረሰተሰብ ክፍሎች)  የሚሳተፉበት ቀጠተኛና ሁሉ አቀፍ ምርጫ ለማድረግ እንኳንስ እንደዚህ ዓይነት መላው ዓለምን ሥጋት ላይ የጣለ ወርሽኝ ባለበት ይቅርና ምርጫ በባህሪው ምርጫ የሚደረግባት አገር በከፍተኛ ደረጃ በተረጋጋ ሁኔታ  ወስጥ መገኘትን ግድ ይላታል፡፡

2.1 ከመሰረታዊ የሕገ-መንግስት የትርጉም መርሆች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት የአርቃቂው ሀሳብ እና  የሕገ-መንገስት ትርጉም ባስፈለገበት ጊዜ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ (present scenario)[8]  ናቸው፡፡ ሕገ-መንግስቱን ያረቀቁት ምንም እንኳን የመንግስት የአምስት ዓመት የሥልጠን ዘመን ማጠናቀቂያ ላይ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ሳይኖር ቢቀር ምርጫው ሊራዘም የሚችል ሰለመሆኑና በምርጫ ዘመን ማጠናቀቂያው ጊዜ አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወስጥ የምትገኘ ከሆነ ምርጫው ሊራዘም የሚችል ስለመሆኑ ምንም ሳይሉ ያለፉት ቢሆንም ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ምርጫው ቀጥኛና አሳታፊ በሆነ ሁኔታ ሊከናወን እንደሚገባው የሕገ-መንግስቱ ፍላጎት ሰለመሆኑ ያንጸባረቁ ስለሆነ  ይህንን መሰረት አድርጎ ክፍተቱን ለመሙላት ሕገ-መንግስቱን መተርጎም ከሕገ መንግስቱ አጠቃላይ መንፈስና ፍላጎት  ማፈንገጥ አይሆንም፡፡  ከዚህም በተጨማሪ አሁን ያለው ሁኔታ ምርጫውን ለማድረግ ፈጽሞ የማያስችል ስለመሆኑ በአጠቃላይ ሕብረተሰቡ የታመነበት ከመሆኑም በላይ ተቃራኒ የፖሊቲካ ዓላማ ያላቸው ወገኖችን ጭምር ያስማማ ነው፡፡ ከዚህም አንጻር ሕገ-መንስግቱን መተርጎም የሕገ-መንገስቱን ዓለማና ግብ ከሚያሳካ በሰተቀር በተቃራነው ሊታይ የሚችል አይደለም፡፡

2.2 ከእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች አኳያ አሁን በሥራ ላይ ያለው  የሕግ አውጪ ም/ቤትና የአሰፈጻሚው አካል  የምርጫ ጊዚያቸው አልፏል ተበሎ ሊበተኑ ስለማይገባ የአስቸኳያ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ምክንያት የሆነው ወረርሽኝ ከተወገደ በኋላ በአንድ ዓመት ጊዜ ወስጥ ምርጫው አንዲደረግ በሚፈቅድ መልኩ ሕገ መንግስቱ ሊተረጎም ይገባል በማለት ይህንን አስተያየቴን አቅርቤያለሁ፡፡

 

 

[1]  የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 38 (1) (ሀ) እና (ሐ)

[2] የሕገ መንግስቱ እንቀጽ 54 (1)

[3] የምርጫ ሕግ አንቀጽ 5 (1)

[4] Article 21 (3) secton  3 of UDHR

[5] Art 25 of ICCPR

[6] Art 13 of ACHPR

[7] ሕገ መንግስት አንቀጽ 58 (3)

[8]