የወንጀል ክስን ማቋረጥና የይቅርታ አሰጣጥን በተመለከተ ሕጉና አተገባበሩ፤

  1. ክስ ማቋረጥን በተመለከተ፤

በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 በአንቀጽ 6 ሥር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሥልጣንና ተግባሩ ተዘርዝሯል፡፡ በዚህም መሰረት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፌዴራል መንግስትን በመወከል የወንጀል ክስ እንደሚመሰረት፣ በፍ/ቤት እንደሚከራከር ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ባገኘው ጊዜ ደግሞ የመሰረተውን ክስ ማንሳት እንደሚችል በአንቀጽ 6 (3) (ሠ) ላይ ተመልክቷል፡፡ ይሄው የተቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሥልጣን የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 40 (5) መሰረት ለፍትህ ሚኒስቴር ተሰጥቷል፡፡ በሌላ በኩልም  በሥራ ላይ ባለው በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ በአንቀጽ 122 ላይ ዐቃቤ ሕግ በከባድ የግፍ ግድያና በከባድ የውንብድና ወንጀል ከተከሰሱ ሰዎች በስተቀር በሌሎች ጉዳዮች የተከሰሱ ሰዎችን ከፍርድ በፊት የፍርድ ቤቱን ፈቃድ በማግኘት ክሱን ማንሳት እንደሚችል ተደንግጓል፡፡  በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ መሰረት ክስ ለማንሳት የፍርድ ቤት ፈቃድ አስፈላጊ ቢሆንም በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ደግሞ ክስ ለማንሳት ዐቃቤ ሕግ የፍ/ቤት ፈቃድ አያስፈልገውም፡፡ በዚህ ረገድ በሁለቱ ሕጎች መካከል ልዩነት ያለ ሲሆን ከሕግ አተረጓጎም መርህ አኳያ በኋላ የወጣ ሕግ ቀድሞ ከወጣ ሕግ ተፈጻሚነት የሚኖረው በመሆኑ ተፈጸሚነት የሚኖረው በኋላ የወጣው የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ይሆናል ማለት ነው፡፡

በዚህ አዋጅ ላይ ተመስርቶም በተለያየ ጊዜ ዐቃቤ ሕግ በተከሰሱ ሰዎች ላይ ያቀረበውን ክስ ሲያነሳ ቆይቷል፡፡ ማንኛውም ሰው መታሰረም ሆነ መፈታት ያለበት በሕግ መሰረት ብቻ መሆን እንደሚገባው የሚታመን ነው፡፡

ከላይ እንደተመለከተው በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ  በአንቀጽ 6 (3) (ሠ) መሰረት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ ለማንሳት ሥልጣን የተሰጠው ክስ ማንሳቱ ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ነው፡፡ የሕዝብ ጥቅም ሲባል እሰከምን ድረስ እንደሆነ በዝርዝር ባይሆንም አመላካች በሆነ ሁኔታ በአዋጁ ትርጉም አልተሰጠውም፡፡ በሌሎች ሕጎችም ቢሆን የሕዝብ ጥቅም ትርጉም ተስጥቶት የሚገኝ ባለመሆኑ ለክርክር የተጋለጠ ነው፡፡ በመሆኑም የክሱ መነሳት የሕዝብን ጥቅም ይመለከታል ወይንስ አይመለከትም የሚለው በራሱ ለክርክር የተጋለጠ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በተለያየ ጊዜ ክስ የሚነሳላቸው ሰዎች በአንድ በኩል ቀድሞውንም ቢሆን ሊከሰሱ የሚገባቸው አልነበሩም የሚል አስተያየት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሊከሰሱና ሊቀጡም ይገባል የሚል አስተያየት ከተለያየ አቅጣጫ ሲነገር እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡

የትኛው ተከሳሽ ንጽሁ ነው የትኛው ደግሞ ጥፋት ፈጽሟል ለሚለው ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ጉዳዩ በነጻ፣ ገለልተኛ፣ ጠንካራና ተገማች በሆነ ፍ/ቤት በተስተካከለ የፍርድ ሂደት (due process of law) አልፎ ነጻ መባል የሚገባው ነጻነቱ ቢረጋገጥ ፣ጥፋት ፈጽሟል የሚባለው ተከሳሽ ደግሞ ጥፋተኛኘቱ በፍርድ ቢረጋገጥ የሕዝብ ጥቅምንም ሆኖ የፍትህ ፍላጎትን (interest of justice) ማሳካት ይቻል ነበር፡፡  እንደዚሁም መንግስትም በዳኝነት ነጻነት እና የሕግ የበላይነት መርህ ላይ ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋግጥ ነበር፡፡  

በመርህ ደረጃ ዐቃቤ ሕግ ክሱን ባቋረጠላቸው ሰዎች ላይ የወንጀል ክስ ሲያቀርብ ጥፋተኛነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል በቂ ማስረጃ እንዳለው አምኖ ክሱን አቅርቧል ተብሎ ይገመታል፡፡ ዐቃቤ ሕግ በተደጋጋሚ ጊዜ ያቀረበውን ክስ ሲያነሳ የሚስተዋለው ጉዳዩ በፍቤት ክርክር ረዘም ያለ ጊዜ ካሰቆጠረና አንዳንድ ጊዜም የማስረጃ ማሰማት ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ ሲሆን በአንዳንድ ጉዳዮች ደግሞ የማስረጃ ማሰማት ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ነው፡፡ የተከሰሱ ሰዎች ንጽሕና ወይንም ጥፋተኛነት በፍርድ ከመረጋገጡ በፊት የዐቃቤ ሕግ ክስ ማንሳት የሕዝብ ጥቅምንም ሆነ የፍትህ ፍላጎትን የሚጎዳ ነው፡፡ በእርግጥ ዐቃቤ ሕግ ከፍርድ በፊት በማናቸውም ጊዜ ክስ ለማነሳት በሕግ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ክስ በሚያነሳበት ጊዜ ግን የሕዝብ ጥቅምና የፍትህ ፍላጎትን በሚጎዳ ሁኔታ መሆን የለበትም፡፡ ዐቃቤ ሕግ ክርክሩን ቀጥሎ ክሱን በበቂ በማስረጃ ባለማረጋገጡ ምክንያት በፍ/ቤት ውሳኔ ነጻነታቸው ተረጋግጦ ከእስር መለቀቅ የሚገባቸው ሰዎች ከመለቀቃቸው በፊት ክስ በማንሳት ከእስር እንዲፈቱ ማድረግ ውጤቱ መልካም ቢሆንም ነገር ግን ተከሳሾች ፍትህ አግኝተዋል ማለት አይቻልም፡፡ እርምጃው የሕዝብ ጥቅምንም ሆነ የፍትህ ፍላጎትን ያሳከ ነው ለማለትም አያስደፈርም፡፡ በፍ/ቤት ነጻነነቱ ተረጋግጦለት ከእስር የሚለቀቅ ሰውና በዐቃቤ ሕግ በኩል ክሱ የተነሳለት ሰው አኩል አንገታቸውን ቀና አድርገው ሊሄዱ የሚችሉ ሰዎች አይሆኑም፡፡ ምክንያቱም በፍርድ ቤት በነጻ የተለቀቀ ወይም የተቀጣ ሰው በዚያው ጉዳይ በድጋሜ እንዳይከሰስ (prohibition of double jeopardy) ሕገ-መንግስታዊ ጥበቃ ጭምር ያለው በመሆኑ ነው፡፡ የሕገ-መንግስት አንቀጽ 23 ይመለከታል፡፡ ክስ የተነሳለትን ሰው በተመለከተ ግን ተመልሶ ሊከሰስም የሚችልበት አጋጣሚ ስለሚኖር ነው፡፡ አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6 (3) (ሠ) ይመለከታል፡፡

ከሕዝብ ጥቅምም ሆነ ከፍትህ ፍላጎት አንጻር ክስ ከመመስረቱ በፊት ጉዳዮ በጥንቃቄ ቢታይና ቢመረመር በጣም የተሻለ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ በረቂቅ ደረጃ ላይ የሚገኘው የወንጀል ሥነ-ሥርዓት አንቀጽ 158 የሕዝብ ጥቅምን መሰረት በማድረግ ለዐቃቤ ሕግ ሥልጣን የሚሰጠው የተመሰረት ክስን ለማንሳት ሳይሆን ገና ከመነሻው ክስ ላለመመስረት ነው፡፡ የሕዝብ ጥቅም ሲባል አድማሱ እስከምን ድረስ ነው የሚለው ለትርጉም የተጋለጠ በመሆኑ ይህንን ለማስወገድ በማሰብ ረቂቅ ሕጉ የሕዝብ ጥቅምን ወሰን በተሻለ ሁኔታ ዘርዘር አድርጎ በመግለጽ በተቻለ መጠን ለትርጉም እንዳይጋለጥ አድርጎታል ማለት ይቻላል፡፡

በሌላ በኩልም በሙስና ወንጀል የተከሰሱ ሰዎች በሙስና ወንጀል ምክንያት ተገኝቷል የተባለን ገንዘብ ለመንግስት ገቢ እንዲያደርጉ እየተደረገ ክስ ተነስቶላቸው ከእስር እንዲፈቱ የተደረጉ ሰዎች እንደነበሩም የሚታወቅ ነው፡፡  ይሄ ግን ፍጹም ሕግን መሰረት ያደረገ አይደለም፡፡ ግለሰቦቹ መከሰስ የሚገባቸው ሰዎች ካልሆኑ ከመነሻወም ቢሆን ክስ ሊቀርብባቸው አይገባም ነበር፡፡ በሙስና ድርጊት የተገኘ ነው የተባለ ገንዘብ በትክክልም በሙስና የተገኘ ስለመሆኑ በፍርድ ተረጋግጦ ተከሳሾቹ ጥፋተኛ ተብለው ሳይቀጡ ገንዘቡን እንዲከፍሉ በማድረግ ከእስር እንዲፈቱ ማድረግ የፍትህ ፍላጎትን የሚጻረር ነው፡፡    በሙስና የሚከሰሱ አብዛኛዎቹ ተከሳሾች የሚከሰሱት ዋስትና በማያስፈቀድ አንቀጽ በመሆኑ ዋስትና ተከልክሎ በእስር ላይ የሚገኝ ተከሳሽ የፍርድ ሂደቱ ቀልጣፋ ካለመሆኑ ጋር ተዳምሮ ከተራዘም እስር የተጠየቀውን ገንዘብ በመክፈል ከእስር መፈታትን ስለሚመረጥ ወደዚህ ተግባር እንዲገባ የሚገፋፋ ነው፡በመሆኑም ጥፋተኛ መባል የሚገባው ሳይፈረድበት ንጽሕናውም በፍርድ ሊረጋገጥለት የሚገባው ሳይረጋገጥለት በሙስና ወንጀል ተገኝቷል የተባለን ገንዘብ እንዲከፍል በማድረግ ክስ በማንሳት ከእስር እንዲፈታ ማድረግ ሕግን መሰረት ያደረገ አይደለም፡፡ በፍርድ ጥፋተኛ ቢባል ገንዘቡ የሚወረስ ስለመሆኑም መዘንጋት የሌለበት ነው፡፡ በመሆኑም የዚህ ዓይነቱ  የሕዝብ ጥቅምንም ሆነ የፍትህ ፍላጎትንም የሚያስጠብቅ አይደለም፡፡

ሲጠቃለልም እኔ በተረዳሁት ልክ ዐቃቤ ሕግ በአንዳንድ ጉዳዮች ክስ የሚያነሳበት አግባብ የሕዝብ ጥቅምን እና/ወይም የፍትህ ፍላጎትን አሳክቷል ለማለት ስለማይቻል በሕጉና ባተገባበሩ መካከል አለመጣጣም እንዳለ መገንዘብ ይቻላል፡፡ The withdrawal of charge should be justified and documented to maintain public trust. Arbitrary or unexplained withdrawals could undermine confidence in the justice system.

  • ይቅርታን በተመለከተ፤

ስለ ይቅርታ ከማንሳታችን በፊት በቅድሚያ ዐቃቤ ሕግ ሕጉን መሰረት አድርጎ በፍ/ቤት ለማስቀጣት የሚያስችል በቂ ማስረጃ አለኝ ብሎ ሲያምን ክስ ማቅረብ እንዳለበት የሚታመን ነው፡፡  ዐቃቤ ሕግ በቂ ማስረጃ አለኝ ብሎ ክስ ካቀረበም የክስ ሂደቱ በነጻ፣ ገለልተኛና ጠንካራ ፍ/ቤት በተስተካከለ የፍርድ ሂደት ሊያልፍ ይገባል፡፡ ይህም ማለት ተከሳሹ በአገሪቱ ሕገ-መንግሰት፣ በወንጀል ሕጉ፣ አገሪቱ ተቀብላ የሕጓ አካል ባደረገቻቸው ዓለም ዓቀፍና አህጉራዊ ሰምምነቶች የተረጋገጡ መሰረታዊ መብቶቹ ሊከበሩለት ይገባል ማለት ነው፡፡ የተከሳሹ መሰረታዊ መብቶች ተከብረው ጉዳዩ በተስተካካለ የፍርድ ሂደት አልፎ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ማስረጃ ከምክንያታዊ ጥርጣሬ በጸዳ ሁኔታ ክሱን አስረድቶ ተከሳሹ በመከላከያ ማስረጃው የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ ማስተባበል ሳይችል በመቅረቱ ጥፋተኛ ተብሎ የቅጣት ውሳኔ ሊተላለፈበት ይገባል፡፡

በይቅርታ አሰጣጥና ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 840/2006 መሰረት የተፈረደበት ሰው በይቅርታ ለመፈታት ፍላጎት ካለው በይቅርታ ሊፈታ ይችላል፡፡ ይቅርታውም መብት ሳይሆን ዕድል (privilege) ነው፡፡ የይቅርታ ጥያቄው መስተናገድ የሚችለውም የቅጣት ፍርዱ ከተሰጠ በኋላ በማናቸውም ጊዜ ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 17 (1) ላይ ተመልክቷል፡፡ የይቅርታ ቦርድም የቀረበለትን አቤቱታና ማስረጃ መርምሮ ፍርደኛው ለይቅርታ ብቁ መሆኑን ካመነ ከመግለጫ ጋር ለአገሪቱ ፕሬዝዳንት አቅርቦ ፕሬዝዳንቱ የቀረበለትን መግለጫ መሰረት በማድረግ የመጨረሻውን የይቅርታ ውሳኔ እንደሚሰጥ በአንቀጽ 21 ላይ ተመልክቷል፡፡

ይቅርታን በተመለከተ ሕጉ የሚለው ከሞላ ጎደል ከላይ የተመለከተውን ነው፡፡ አተገባበሩን በተመለከተ በአንድ ወቅት (ከ7 ዓመት በፊት) ሕጉን መሰረት አድርጎ እንደማይተገበር የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በግሌ ታዝቤያለሁ፡፡

የመጀመርያው ያተገባበር ችግር የሚጀምረው በፍትህ ሚኒስቴር ሲሆን ከላይ እንደተጠቀሰው በአዋጁ አንቀጽ 17 (1) መሰረት የቅጣት ውሳኔ የተላለፈበት ፍርደኛ በማናቸውም ጊዜ የይቅርታ አቤቱታ ማቅረብ እንደሚችል ተደንግጎ ባለበት ሁኔታ ነገር ግን በፍትህ ሚኒስቴር በኩል ወጥቷል በተባለ መመርያ ፍርደኛው የተፈረደበትን 1/3ኛ ፍርድ ካልፈጸም የይቅርታ ጥያቄ ማቅረብ አይችልም በማለት የይቅርታ አቤቱታ ውድቅ እንደሚደረግ ታዝቤያለሁ፡፡  

አዋጁን ለማስፈጸም የሚኒስትሮች ም/ቤት ደንብ እንደሚያወጣ የይቅርታ ቦርድ ደግሞ አዋጁንና ደንቡን ለማስፈጸም የሚያስችል መመርያ እንደሚያወጣ በይቅርታ አዋጁ በአንቀጽ 28 (1) እና (2) ላይ ተመልክቷል፡፡ የይቅርታ ቦርድ መመርያ ለማውጣት በአዋጁ ሥልጣን የተሰጠው በአዋጁ ማዕቀፍ ውስጥ በመሆን እንጂ ከአዋጁ በመውጣት በመጨመር ወይንም በመቀነስ ሊሆን አይችልም፡፡ ቅጣት የተወሰነበት ፍርደኛ በማናቸውም ጊዜ የይቅርታ ጥያቄውን ለቦርዱ ማቅረብ እንደሚችል በአዋጁ ላይ በግልጽ ከተደነገገ ፍርደኛው ከእስር ጊዜው 1/3ኛውን የታሰረ ከሆነ ብቻ ጥያቄውን ማቅረብ ይችላል የሚል መመርያ ማወጣቱ ሕጉን በግልጽ የሚጻረር ብቻ ሳይሆን የመንግስት የሥልጣን ክፍፍል መርህንም የሚጥስ ነው፡፡ ይህ አንደተጠበቀ ሆኖ የጽሁፉ አቃራቢ በቦርዱ ወጣ የተባለን መመርያ ለመመልከት ጥረት አድርጎ የነበረ ሲሆን መጨረሻ ላይ የተገለጸለት በቦርዱ የወጣ መመርያ እንደሌለና ውሳኔው የተላለፈው በወቅቱ የነበሩ የፍትህ ሚኒስተር ጽፈውታል በተባለ የሰርኩላር ደብዳቤ እንደሆነ ተገልጾልኛል፡፡ እንግዲህ አዋጁ በመመርያም ሳይሆን ከዚያም ወርዶ በሚኒስትሩ የሰርኮላር ደብዳቤ ተሸሯል ማለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ጉዳይ ገጥሞኝ ወደ ፍትህ ሚኒሴቴር ስላልሄድሁ ይህ አሰራር መለወጥ አለመለወጡን አላውቅም፡፡

ይቅርታን በተመለከተ የሚስተዋለው ሌላ ሕግን ያልተከተለ አሰራር በይቅርታ አዋጁ አንቀጽ 15 መሰረት ይቅርታ ለማድረግ በቅድሚያ የይቅርታ አቤቱታ ይቅርታ እንዲደርግለት በሚፈልገው ፍርደኛ ሰው ዓማካይነት ለቦርዱ መቅረብ ያለበት ሲሆን ግለሰቡ ይቅርታ እንዲደረግለት ካላመለከተ ወይም ካልፈለገ በይቅርታ ሊፈታ አይችልም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ይቅርታ ሳይጠይቁ ሲፈቱ ይታያል፡፡ ለመጠቀስም ያህል በ2010 ዓ.ም አቶ አንዱዓለም አራጌና አቶ አስክንደር ነጋ ከእስር የተፈቱት ይቅርታ ሳይጠየቁ እንደሆነ ከራሳቸው አንደበት ሰምተናል፡፡ የግለሰቦቹ መፈታት ውጤቱ መልካም ቢሆንም ነገር ግን ሕጋዊ በሆን መንገድ ተፈተዋል ለማለት ግን አይቻልም፡፡ ይቅርታ የጠየቀ ሰው ለይቅርታው መሟላት የሚገባቸውን አሟልቶ ለቦርዱ ሲያመለክት ቦርዱ አስፈላገውን ማጣርት አድርጎ ግለሰቡ ለይቅርታ ብቁ ነው ካለ ከመግለጫ ጋር ለመጨረሻ ውሳኔ ለአገሪቱ ፕሬዝዳንት አቅርቦ ፕሬዝዳንቱ የመጨረሻ የሆነውን የይቅርታ ውሳኔ ሰጥቶ ግለሰቡ ፍ/ቤት መቅረብ ሳያስፈለገው ከእስር አንዲፈታ ይደረጋል፡፡ ነገር ግን በፍርድ ቤት ውሳኔ በእስር ላይ የሚገኝን ሰው ይቅርታ ሳይጠይቅና ጉዳዩ በይቅርታ ሥነ-ሥርዓት ሳያልፍ መፍታት የይቅርታ አዋጁን በግልጽ የሚጻረር ከመሆኑም በላይ በፍ/ቤት ውሳኔም የታሰረን ሰው ያለ ፍ/ቤት የመፈቻ ትዕዛዝ እንዲፈታ ማድረግ የፍ/ቤቱንም ሥልጣን የሚጋፋ ነው፡፡

ይቅርታን በተመለከተ በሕጉና ባተገባበሩ መካከል ያለውን አለመጣጣም በተመለከተ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ ቢኖር በ1997 ዓ.ም የተደረገውን ምርጫ ተከትሎ በተነሳው ሁከት በወቅቱ ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ተብሎ ይታወቅ የነበረ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የነበሩ ሰዎች ተይዘው ከታሰሩ በኋላ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት እነ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል በሚል መዝገብ ክስ ቀርቦባቸው በእሥር ላይ ሆነው የፍ/ቤት ክርክሩ 2 (ሁለት) ዓመት የሚጠጋ ጊዜ ወስዶ ነበር፡፡ ከዚያም በ1999 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ሰኞ ቀን ዕድሜ ልክ ተፈርዶባቸው በዚያው ሳምንት ዓርብ ቀን በይቅርታ ተፈተዋል፡፡ የተፈረደበት ሰው በይቅርታ ሊፈታ የሚችለው ከላይ እንደተጠቀሰው የይቅርታ ፎርም ሞልቶ ከዝርዝር መግለጫና ማስረጃ ጋር አደራጅቶ ለቦርዱ በማቅረብ ነው፡፡ ቦርዱ ደግሞ የተለያዩ መ/ቤቶች ኃላፊዎችን በአባልነት ያቀፈ እንደመሆኑ መጠን ኃላፊዎቹ ተሰባስበው ይቅርታውን መርምረው ፍርደኛው ይቅርታ የሚገባው መሆኑን ካመኑ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት ያስተላለፍሉ፡፡ በይቅርታ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት በተግባር ረጅም ወራትን መጠበቀ ግድ በሆነበት ሁኔታ ሰኞ ቀን ዕደሜ ልክ የተፈረደባቸው የቅንጀት አመራሮች ከ 3 (ሶስት) ቀን በኋላ ዓርብ ቀን በይቅርታ ሊፈቱ የሚችሉበት አግባብ የለም፡፡ እውነታው ይሄ ከሆነ እንዴት ሊፈቱ ቻሉ የሚለው ሲታይ ይቅርታ የተደረገላቸው ጉዳዮ በሕግ የተቀመጠውን ሥርዓት ተከትሎ ሳይሆን ጉዳያቸው ገና በፍ/ቤት በቀጠሮ ላይ እያለ ጥፋተኛ ከመባላቸወና የቅጣትም ውሳኔ ሳይወሰንባቸው የይቅርታ ሰነድ አስቀድሞ እንዲፈርሙ ስለመደረጋቸው መገመት አያዳግትም፡፡ ግለሰቦቹ የይቅርታ ሰነድ እንዲፈርሙ ከተደረገ በኋላ በዚያው አልተለቀቁም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ መጠበቅ ግድ ስለሆነ ነው፡፡ የፍ/ቤቱ ውሳኔም የተፈለገው ጥፋተኛነታቸው በፍርድ ተረጋግጦ ተቀጥተዋል ለማለት እንዲቻል ለይስሙላ የተደረገ ፖሊተካዊ ዘዴ መሆኑን መገመት አያዳግትም፡፡ ፍ/ቤትን በዚህ ደረጃ ማውረድ ጉዳቱ በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ በቻ ሳይወሰን አገርንም እንደ አገር የሚጎዳ ተግባር ነው፡፡

ማጠቃለያ

ክስን ለማቋረጥም ሆነ ይቅርታ ለማድረግ በቅድሚያ የወንጀል ክስ የሚቀርብበት ሰው የተጠረጠረበትን ወንጀል ስለመፈጸሙ ከምክንያተዊ ጥርጣሬ የጸዳ ማሰረጃ ሊኖር ይገባል፡፡ ይህ መርህ ዓለም የተቀበለው መርህ ነው፡፡ በወንጀል ጉዳይ የመጀመርያው ዳኛ ዐቃቤ ሕግ ነው፡፡ ዐቃቤ ሕግ በተጠርጣረው ላይ የተጣራውን የምርምራ መዝገብ በነጻነት መርምሮ ክስ ለማቅረብ የሚያስችል በቂ ማስረጃ የለም ብሎ ካመነ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 42 (1) (ሀ) ላይ እንደተመለከተው ክስ አይቀርብም ብሎ ለመወሰን ሙሉ የሆነ የሙያ ነጻነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ማስረጃ እያለው አትክሰስ ወይንም በተቃራኒው ማሰረጃ ሳይኖር ክሰስ የሚል ትዕዛዝ ከዬትኛወም አቅጣጫ ሊመጣ አይገባም፡፡ ዐቃቤ ሕግ የማንውኛም አካል ማሺነሪ መሆን የለበትም፡፡

በረቂቅ ደረጃ የሚገኘው የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ዐቃቤ ሕግ የሙያ ነጻነት ሊኖርው እንደሚገባ በግልጽ ደንግጓል፡፡ ተጠርጣሪው ድርጊቱን ስለመፈጸሙ ማስረጃ ቢኖርም የተፈጸመው ድርጊት ወንጀልን የሚያቋቁሙ ሁኔታዎች ከሌሉ ሊከሰስ እንደማይገባ ደንግጓል፡፡ ዐቃቤ ሕግ በቂ ማሰረጃ አለኝ ብሎ ክስ ካቀረበ በኋላም ጉዳዩ በተስተካከለ ሂደት ማለፍ አለበት፡፡ በተስተከከለ የፍርድ ሂደት አልፎ በቂ ማስረጃ ቀርቦበት በመከላካያ ማስረጃው ማስተባበል ሳይችል ቀርቶ ጥፋተኛ ተብሎ ቅጣት የተወሰነበት ፍርድኛ ብቻ ነው በይቅርታ መፈታት የሚገባው፡፡ ነገር ግን ገና ከመነሻው ሊከሰስ የሚይገባውና ከተከሰሰም በኋላ በነጻ ሊሰናበት ሲገባው ጥፋተኛ ተብሎ የተቀጣን ሰው በይቅርታ እንዲፈታ ማደረግ የሕዝብ ጥቅምንም ሆነ የፍትህ ፍላጎትን አሳክቷል ማለት አይቻልም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *